የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ፕሮግራሞች ክትትልና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ለአባያ፣ ጫሞና ሳውላ ካምፓስ የካውንስል አባላት፣ ከየትምህርት ክፍሉ ለተወጣጡ ነባር መምህራን፣ ለተማሪ ተጠሪዎች እና ለፕሮግራም ዕውቅና ኮሚቴ አባላት የፕሮግራም ዕውቅና ሥራን አስመልክቶ ከታኅሣሥ 10-12/2017 ዓ/ም ገለጻ አድርጓል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም የትምህርት ጥራት በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ለማሳካት በዩኒቨርሲቲዎች የሰው ኃይል፣ ዕውቀት እና መረጃ የማግኘት አቅም ያለ በመሆኑ ይህን አቀናጅተን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ክትትልና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሠረቀብርሃን ታከለ ገለጻው በሀገር ውስጥ ዕውቅና ያገኙ ፕሮግራሞች ይዘት፣ የፕሮግራም አቀራረጽ፣ ዕውቅና የሚያገኙበት መንገድና መሰል ይዘቶች ላይ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንደ ዩኒቨርሲቲ ካሉን 75 የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች 15ቱ በ2017 ዓ/ም ሀገር አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኙ ታቅዷል ብለዋል፡፡
የተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ኤፍሬም ጌታሁን እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው ያሉ ፕሮግራሞች አስፈላጊውን ሒደት ጠብቀውና መስፈርቱን አሟልተው በኢትዮጵያ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን (ETA) ዕውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ ገለጻው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ በበኩላቸው እንደ ሀገር የተሠሩ ሪፎርሞችን መሠረት አድርጎ የትምህርት ጥራትና አግባብነትን ለማረጋገጥ የፕሮግራም ዕውቅና ሥራ የሚተገበር ሲሆን ይህንን ለማሳካት ኮሌጁ መምህራንን በማስተባበርና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አበራ ኡንቻ በ2017 ዓ/ም በኮሌጁ ሁለት ፕሮግራሞች ዕውቅና እንዲያገኙ መሥራት እንዳለብን በዩኒቨርሲቲው ሴኔት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በኮሚቴ የተመደቡ መምህራን በአግባቡ ሥራውን እንዲሰሩ አስፈላጊው ድጋፍ በኮሌጁ በኩል ይደረጋል ብለዋል፡፡
የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የድኅረ ምረቃ ትምህርትና የምርምር አስተባባሪ ዶ/ር ሙሉጌታ ሐብቴ ከገለጻው በኋላ በሰጡት አስተያየት የፕሮግራም ዕውቅና ለማግኘት እንደ ቤተ ሙከራና ቤተ መጻሕፍት ያሉ ግብአቶች ቀድመው ዕውቅና ቢያገኙ ሥራውን የሚያቃልል በመሆኑ ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራ የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት