አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የአርባ ምንጭ ቃል ኪዳን ቤተሰብ ምሥረታ መርሐ ግብር ታኅሣሥ 03/2018 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዕለቱ የክብር እንግዳ የሰላም ሚኒስትር ተወካይ ወ/ሮ ዮዲት ከበደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሰላምን ለማምጣት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው ሰላም በዘላቂነት እንዲሰፍን ማኅበራዊ የትስስር ገጾች እና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ጉልህ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ በስፋት እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡ የሰላም ዋጋ ተመን የሌለው መሆኑን ያስታወሱት ወ/ሮ ዮዲት የመረጃ ልውውጣችን ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የቃል ኪዳን ቤተሰቡ ዓላማ ሰዎች በሙሉ ፈቃዳቸው አዲስ ገቢ ተማሪዎችን እንደ ልጆቻቸው በቅርበት ለመከታተል ስምምነት የሚገቡበት መሆኑን ያብራሩት ወ/ሮ ዮዲት በዚህ መሠረት ለተማሪዎች ክትትልና ድጋፍ የሚያደርጉበትን የውል ስምምነት ወላጆቹና ተማሪዎቹ መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡ ተወካይዋ በልጆቹ ላይ የሚዘራው በጎነት የሚናፈቀውን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው ሁሉም ሰው ለበጎ ተግባር ፈቃዱን ማዋልና ሰላምን በቤቱ መሾም እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር አብደላ ከማል የሰላም ሚኒስቴር ባዘጋጀው የቃል ኪዳን ቤተሰብ ፕሮጀክት ሀገራዊ ውይይት ቀደም ብሎ ማድረጋቸውን አስታውሰው  የአብሮነት ዕሴቶች ተጠብቀው እንዲለሙና ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ጉልህ መሆኑን በውይይቱ ላይ ግንዛቤ ማዳበራቸውን ተናግረዋል፡፡

ቤተሰባዊ ትስስር የመፍጠር ሥራው በከተማው ማኅበረሰብና በዩኒቨርሲቲው አዲስ በሚገቡ ተማሪዎች መካከል ጥብቅ ትስስር በመመሥረት በከተማዋ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በመፍጠር ስኬታማ የሀገርና የወገን መከታ የሚሆኑ ምሩቃንን ለማፍራት ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ገልጸው ወጣቱ የማይተካ ሚና ያለው እንደመሆኑ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከፋፋይ ከሆኑ ዘገባዎች እንዲርቁና አንድነት ላይ የሚያተኩሩ ይዘቶችን እንዲያሰራጩ መሥራት እንደሚጠበቅ ለወላጆች አሳስበዋል፡፡  

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶ/ር መስፍን መንዛ መርሐ ግብሩ ግዙፍ ማኅበራዊ ፋይዳ ያለው ኩነት መሆኑን ገልጸው ሰው ተኮር የሆነ ሰብአዊ ተግባር የምናከውንበትና የበጎነት ዐሻራ የምናኖርበት ዕድል በመሆኑ እንደ ከተማ ትልቅ ኃላፊነት የምንቀበልት ነው ብለዋል፡፡ የቃል ኪዳን ቤተሰብ ትስስር ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን የገለጹት ዶ/ር መስፍን ትስስሩ ምቹ የመማር ማስተማርና የምርምር ከባቢን መፍጠር እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡ የቋንቋና የባህል ዕሴቶች ልውውጥና የእርስ በእርስ ትውውቅ ለማድረግ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን የተናገሩት ከንቲባው ይህን ሠናይ ተግባር የከተማው አስተዳደር ከዩኒቨርሲቲው ጎን በመሆን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደተናገሩት የአርባ ምንጭ ቃል ኪዳን ቤተሰብ ምሥረታ ዩኒቨርሲቲውና ከተማ አስተዳደሩ በጋራ የሚሠሩት የማኅበረሰብ አገልግሎት አንድ አካል መሆኑን ያመላከተ ነው፡፡ እሳቤውም ዘርፈ ብዙ የሆነ ጠቀሜታ ያለው ነው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ  ቅንጅታዊ አሠራርን በመዘርጋት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡ ውሉ ከታሰበውና ከዕቅድ በላይ በመሳካቱ ልባዊ ደስታ እንደተሰማቸው በመግለጽ ለስኬቱ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተማሪ ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ሶፎንያስ ፋንታሁን በምሥረታው መደሰቱን ገልጾ ጥሩ ጅማሮ መሆኑንና በአካባቢው ያለውን ሰላም የሚያጸና ብሎም በተማሪዎቹ ዘንድ የሚፈጠረውን የብቸኝነት ስሜት የሚቀርፍና እንደ ሀገርም የሚስተዋለውን የሰላም እጦት ለመፍታት አጋዥ እንደሚሆን ያለውን እምነት ገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ፣ የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የሲቀላ ክፍለ ከተማ ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳምሶን ገመዳ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ወ/ሮ ሀቢባ እንድሪስና ሌሎች የቃል ኪዳን ቤተሰብ መቀላቀላቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው መርሐ ግብሩ በርካታ ተማሪና ወላጅ የተፈጠረበት መድረክ በመሆኑ ለዩኒቨርሲቲውና ለከተማዋ ገጽታ ግንባታና ለማኅበረሰብ ትስስር ጉልህ ዐሻራ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቃል ኪዳን ቤተሰብ ተሳታፊ ተማሪዎች በበኩላቸው ተተኪ የቃል ኪዳን ወላጅ ማግኘታቸው በእጅጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸው በትምህርት ቆይታቸው ባይተዋርነት እንደማይሰማቸውና ጥሩ ቤተሰባዊ ግንኙነት እንደሚያዳብሩ ተናግረዋል፡፡  

በመርሐ ግብሩ የቃል ኪዳን ቤተሰብ ዓላማ እንዲሁም ከተማሪዎቹ፣ ከወላጆች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት እና ከኮሚቴው በቀጣይ ሥራዎች ምን እንደሚጠበቅ የሚያብራራ ሰነድ የቀረበ ሲሆን የቃል ኪዳን ቤተሰብ ተማሪዎችና ወላጆች መካከል የውል ስምምነት በመፈራረም እንዲሁም ሀገር አቀፍ ውድድር ላይ ተሸላሚ ለነበሩ ተማሪዎች የዕውቅና ሰርተፊኬት በመስጠት መድረኩ ተጠናቋል፡፡

በመርሐ ግብሩ የሰላም ሚኒስትር ተወካይ፣ የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ፣ የአርባ ምንጭ ከተማ ሕዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ፣ የአርባ ምንጭ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት፣ የመንግሥት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጋሞ አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝደንት ጨምሮ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ፣ የተማሪ ኅብረትና የሰላም ፎረም አባላት ታድመዋል፡፡


ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት