የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ከዩኒቨርሲቲው አካዳሚክና አስተዳደር ሠራተኞች ጋር በዩኒቨርሲቲው የሪፎርም አጀንዳዎችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መስከረም 27/2018 ዓ/ም ውይይት አካሂደዋል፡፡ በመንግሥት ለዩኒቨርሲቲው የተሰጡ የሪፎርም አጀንዳዎች ዙሪያ እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎች፣ ዩኒቨርሲቲው ከሪፎርም አጀንዳዎች አንጻር አሁን ያለበት ደረጃና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች የውይይቱ ዋነኛ አጀንዳዎች ናቸው።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል በመንግሥት የተሰጡንን የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች መፈጸም እንደ ተቋም የመቀጠል የሕልውና ጉዳይ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። ጊዜው የውድድርና የፉክክር መሆኑን ያወሱት ፕሬዝደንቱ በተቋሙ ተግባራዊ እየሆኑ የሚገኙ የሪፎርም አጀንዳዎችን የጋራ በማድረግ በትብብርና በትጋት ሠሰርቶ ተቋሙን ውጤታማ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሰቲው በተቻለ አቅም ለሠራተኞች ምቹ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር ይሠራል ያሉት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ዕቅድን መሠረት በማድረግ የተሰጡ ተግባራትን የሥራ ሰዓታቸውን በአግባቡ በመጠቀም ሊፈጽሙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። እንደ ዩኒቨርሲቲ በአካዳሚኩም ሆነ በአስተዳደር ዘርፍ ኮሌጆች፣ ሥራ ክፍሎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የተሰጧቸውን ተግባራት በአግባቡ እየፈጸሙ ስለመሆናቸው በየጊዜው አስፈላጊው ክትትልና ግምገማ እንደሚደርግ ያስረዱት ፕሬዝደንቱ ሥራቸውን በአግባቡ የፈጸሙ ዕውቅና የሚሰጣቸው ሲሆን በተቃራኒው የተሰጣቸውን ኃላፊነትና ተግባር ባልተወጡ አካላት ላይ አስፈላጊው ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።
የምርምር ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በዩኒቨርሲቲው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሪፎርም አዋጅን መሠረት በማድረግ ከተቋማዊ ራስ ገዝነት፣ የመስክ ልየታ፣ የትምህርት ጥራት፣ የሥርዓተ ትምህርትና አካዳሚክ መመሪያዎች ዝግጅትና ክለሳ፣ ዲጂታላይዜሽን፣ ምርምር እና አክሪዲቴሽን አንጻር እየተከናወኑ የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎችን በዝርዝር አቅርበዋል። ዶ/ር ተክሉ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን የሚያስችሉ የተለያዩ ፖሊሲዎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ዝግጅቶችና ክለሳዎች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመው የዩኒቨርሲቲውን የምርምር የትኩረት ጭብጦች(Thematic Areas) የመከለስ ሥራ መሠራቱን በገለጻቸው አስረድተዋል።
ከትምህርት ፕሮግራሞች በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ቤተ ሙከራዎች፣ የምርምር ማዕከላትና የምርምር ጆርናሎች አክሪዲቴሽን እንዲያገኙ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ተክሉ በ2017 በጀት ዓመት በሁለት የትምህርት ፕሮግራሞች ሀገር አቀፍ አክሪዲቴሽን መገኘቱ ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።
ሃምሳ ከመቶ የዩኒቨርሲቲው መምህራን 3ኛ ዲግሪ ያላቸው እንዲሆኑ ማስቻል፣ የትብብር ፕሮጀክቶች ቁጥርን መጨመር፣ የ2ኛ እና 3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ቁጥር መጨመር፣ ከሌሎች ተቋማት ጋር የጋራ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችን መክፈት፣ አድቫንስድ የትምህርትና የምርምር ፋሲሊቲዎችን ማደራጀት፣ ንጹሕና አረንጓዴ ካምፓስ መፍጠር እና ሌሎች ከሪፎርሙ ቀጣይ ትኩረቶች መካከል መሆናቸውን ዶ/ር ተክሉ አብራርተዋል::
የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገብረማርያም እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ ሃምሳ ከመቶ መምህራን 3ኛ ዲግሪ ያላቸው ሊሆኑ እንደሚገባ የተቀመጠውን ስታንዳርድ ለማሳካት ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸው መምህራንም ይህን ስታንዳርድ ማሟላት የተቋሙና የራሳቸው የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ተገንዘብው ለትምህርት ራሳቸውን ሊያዘጋጁ እንደሚገባ አስረድተዋል። በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዝ ትምህርት መስጠት ከሪፎርም አጀንዳዎች መካከል ዋነኛው ነው ያሉት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ መምህራን ከሥልጠና ባሻገር የኦንላይን ወይም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዝ ትምህርትን ተግባራዊ ማድረግ መጀመር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ጳውሎስ ታደሰ በዩኒቨርሲቲው በመንግሥት ተግባራዊ እንዲሆኑ የተሰጡ የሪፎርም ሥራዎችን ተግባራዊ ለማድረግና ለመፈጸም የአስተዳደር ሠራተኞች ሚና ጉልህ በመሆኑ በዘርፉ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሪፎርም ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። ዘመኑ የውድድር ነው ያሉት ፕ/ር ጳውሎስ ዩኒቨርሲቲው ተወዳዳሪ እንዲሆን ዕቅድን መሠረት በማድረግ ውጤት ተኮር ሥራ መሥራትና የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ም/ፕሬዝደንቱ ከሰዓት አጠቃቀም ጋር እንደ ተቋም የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አዲስ የሥራ ሰዓት አጠቃቀም የውስጥ መምሪያ ተዘጋጅቶ ከጥቅምት 1/2018 ዓ/ም ጀምሮ ሌሎች የሪፎርም ሥራዎችን በማካተት ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምርም አውስተዋል፡፡
የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ ኢንተርፕርነሪያል ዩኒቨርሲቲ መሆንና ተቋማዊ የሥራ ባህል በራስ ገዝነት ጉዞ ውስጥ ያላቸውን ሚና በማስመልከት ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የመማር ማስተማርና ምርምር ሥራዎች በኢንተርፕርነርሽፕ የሚመሩ መሆን አለባቸው ብለዋል።
ራስ ገዝ መሆን ለዩኒቨርሲቲው በርካታ መልካም አጋጣሚዎችንና ጸጋዎችን ይዞ የሚመጣ ነው ያሉት ዶ/ር ወንድወሰን ይህንን ዕድል ለመጠቀም የተቋሙ ማኅበረሰብ የመፍጠር አስተሳሰብ (Innovative Mindset) ያለውና ክፍል ውስጥ ከማስተማር ያለፉ ማኅበረሰብጋ መድረስና ማኅበረሰብን መጥቀም የሚችሉ አዳዲስ ግኝቶችንና አሠራሮችን ማፍለቅ የሚችል መሆን አለበት ብለዋል። ‹‹በድሮ መፍትሔ የአሁን ችግር አይፈታም›› ያሉት ዶ/ር ወንድወሰን በዩኒቨርሲቲው የታቀዱ የሪፎርም ሥራዎችን ለመፈጸም ከተለመደው አሠራር መውጣትና በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ዘንድ የሥራ ባህልና የአመለካከት ለውጥ (Cultural and Mindset Shift) ማምጣት የግድ እንደሚል አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
በዕለቱ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በተሳታፊዎች ተነሥተው በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን የውይይቱ ተሳታፊዎች መድረኩ የዩኒቨርሲቲውን የትኩረት አቅጣጫዎች፣ የሪፎርም አጀንዳዎችና አሁናዊ ተቋማዊ ደረጃን እንዲገነዘቡ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል። ሠራተኞቹ ለተቋሙ ውጥኖች መሳካት ከአመራሩ ጎን በመሆን በትብብር ለመሥራትና የበኩላቸውን ለመውጣት ቃል ገብተዋል።
በውይይት መድረኩ የዩኒቨርሲቲው ባልደረቦች ለነበሩትና በቅርቡ ሕይወታቸው ላለፈው ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ እና ወ/ሮ መቅደስ ኃይሉ የኅሊና ጸሎት ተደርጓል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት