የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከጋሞ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራ መምሪያ ጋር በመተባበር ከሙዝ ልጣጭ በሚገኝ ስታርች እና ከዓሣ ቅርፊት በሚገኝ ቺቶሳን ውሕድና የሚበላ ፖሊመር በመጠቀም በአካባቢው የሚገኙ ፍራፍሬዎችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም የሚያስችል ምርምር ውጤትን ወደ ማኅበረሰቡ ለማውረድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የማኅበረሰብ ጉድኝትና የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዘርፎች ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ችግር ፈቺ ምርምሮች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመው በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ኬሚስትሪ ት/ክፍል ተሠርቶ ውጤታማ የሆነው ምርምር ፍራፍሬዎችን ሳይበላሹ ለረዥም ጊዜ በማቆየት የአካባቢውን አርሶ አደር ምርታማ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች የበርካታ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ማፍለቂያ እንደመሆናቸው በኮሌጁ በተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች ተማሪዎች፣ መምህራንና ተመራማሪዎች ምርምር እንደሚያካሂዱ ገልጸዋል፡፡ የምርምር ሥራዎች ሼልፍ ላይ ብቻ እንዳይቀሩና የማኅበረሰቡን ችግር በተግባር የሚፈቱ እንዲሆኑ ይጠበቃል ያሉት ዲኑ ፍራፍሬዎችን ሳይበላሹ ማቆየት የሚያስችለው ምርምር የፍራፍሬ መገኛ የሆነውን አርባ ምንጭና አካባቢው ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በኮሌጁ የኬሚስትሪ ት/ክፍል መምህርትና ተመራማሪ ቤተልሔም አበራ በአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢው ያለው ከፍተኛ የፍራፍሬ ምርት በሙቀትና በተለያዩ ምክንያቶች የሚገጥመውን ብልሽት ለማስቀረት በማለም ምርምሩ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ ከሙዝ ልጣጭ የሚገኝ ስታርች እና ከዓሣ ቅርፊት የሚገኝ ቺቶሳን ውሕድን በመጠቀም በኬሚስትሪና በባዮሎጂ ቤተ ሙከራዎች የተደረገው ምርምር ውጤታማ መሆኑንና ይህንንም ወደ ማኅበረሰቡ ለማድረስ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን ተመራማሪዋ ገልጸዋል፡፡
የኬሚስትሪ ት/ክፍል ኃላፊ መ/ር ኢዮብ ሙሉጌታ መሰል የጥናትና ምርምር ሥራዎች መሠራታቸው እንደ ዩኒቨርሲቲ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው የምርምር ውጤቱ ለአጠቃቀም ቀላል በመሆኑ ተጠቃሚው ማኅበረሰብ በቀላሉ የሚተገብረው ነው ብለዋል፡፡
የጋሞ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራ መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ተመስገን ጎበና እንደገለጹት ዞኑ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት የታወቀ ቢሆንም ተበላሽቶ በሚጣል ምርት ምክንያት ከፍተኛ ብክነት ይከሰታል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ መሰል ምርምሮች ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ያሉት አቶ ተመስገን ምርምሩ ወደ ማኅበረሰቡ ደርሶ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መምሪያው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ ጠቁመዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት