የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ እና የምርምር ዳይሬክቶሬቶች በመተባበር ለጀማሪ ሴት መምህራን ‹‹Basic of Research, Statistical Tools for Data Analysis and Interpretation, Manuscript Writing and the Tricks of the Publishing›› በሚል ርዕስ የምርምር ክሂሎት ማዳበሪያ ሥልጠና ከጥር 23-24/2015 ዓ/ም ሰጥተዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማሪያም ከዚህ ቀደም ለነባር ሴት መምህራን ሥልጠናው መሰጠቱን ጠቁመው ለጀማሪ ሴት መምህራን የተዘጋጀው ሥልጠና የምርምር ክሂሎታቸውን እንዲያዳብሩና መሠረታዊ ዕውቀት እንዲጨብጡ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለሴቶች ምርምር የሚሆን በጀት 50 ሺህ ብር እንደሆነና የሴት ተመራማሪዎች ቁጥር በማነሱ ወንዶችም የሚጠቀሙበት አሠራር እንደነበር ዶ/ር ተስፋዬ ገልጸው አሁን ላይ የሴቶች የምርምር መጠን ከፍ ማለቱንና እስከ 185 ሺህ ብር በጀት መፈቀዱን ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም ሴቶች የተሻለ የበጀት አጠቃቀም ያላቸው በመሆኑና በምርምር ዘርፍ ጠንክረው ቢሠሩ በማስተማር፣ በአመራርነትና የተለያዩ ኅትመቶችን ለማሳተም አቅም እንደሚፈጥር እንዲሁም የተሻለ ዕውቀት በማግኘት ጥራት ያለው ምርምር ለመሥራት የሚያግዝ በመሆኑ ለሴቶች ለየት ያለ ማበረታቻ ማድረግ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቡድን መሪ አቶ ዛፉ ዘውዴ በበኩላቸው የሴቶችን አቅም ማጎልበት የዳይሬክቶሬቱ አንዱ ዓላማ በመሆኑ ሥልጠናውን ለመስጠት መነሳሳታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው ሴቶች ወደ ምርምሩ እንዲመጡና ብቁ ተመራማሪ እንዲሆኑ አቅም የሚያጎለብት ነው ያሉት አቶ ዛፉ ዘመኑ የውድድር እንደመሆኑ ሴት መምህራን ክሂሎታቸውን አሳድገው በራሳቸው የሚተማመኑ፣ በዕውቀት ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዳይሬክቶሬቱ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡

የብዝሃ ሕይወት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርና ‹‹Manuscript Writing›› ላይ ሥልጠና የሰጡት ዶ/ር ሽቴ ጋተው ሥልጠናው ሴት መምህራን ወደ ምርምር እንዲገቡ ለማበረታታትና የሠሩትን ጥናታዊ ጽሑፎች ወደ ኅትመት እንዲቀይሩ የሚገፋፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚድዋይፍሪ ት/ክፍል መምህርት የሆኑት ሠልጣኝ ቤዛዊት አፈወርቅ ሥልጠናው ለማንኛውም መምህር ምርምርን በተመለከተ እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ እንደሆነና የብዙዎቻቸውን ችግር እንደሚቀርፍ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ‹‹Manuscript Writing›› ላይ ብዙ ዕውቀት ማግኘታቸውን ገልጸው ለወደፊትም ጥናታዊ ጽሑፎችን ከመጻፍ በዘለለ ጥናቶቹን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያሳትሙበትን ዕድል እንደሚፈጥር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት