አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚያከናውናቸው ውጤታማ የምርምር ተግባራት የተቋሙን የዓለም አቀፍ እይታ እንዲጨምር ማስቻሉን የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝንት ጽ/ቤት ገልጿል፡፡
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት በኃይሉ መርደኪዮስ (ተ/ባ ፕሮፌሰር) እንደገለጹት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውጤታማነት የሚረጋገጠው ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን በሚከናወኑ ምርምሮች የማኅበረሰቡን ችግር በዘላቂነት በመፍታትና ሀገራዊ የልማት አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ሀገራዊ የልማት አቅጣጫዎችና ተልእኮዎች ላይ ትኩረት በማድረግ እና ጠንካራ የኢንደስትሪ ትስስር በመፍጠር ውጤታማ ምርምሮችን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ ለዚህም ም/ፕሬዝደንቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና በሌሎች እንሰት አብቃይ አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ማረጋገጥና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማሻሻል የሚያስችል ምርምርና የእንሰት ቴክኖሎጂዎች ፈጠራና ሽግግርን እንዲሁም የማዕድን አለኝታ ጥናቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲውና ማኅበረሰቡ በፈጠሩት የጉድኝት እሳቤና የማኅበረሰቡን የመልማት ጥያቄ መሠረት በማድረግ በተለያዩ የገጠር ቀበሌያት በሚገኙ ት/ቤቶችና የጤና ተቋማት የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግና የመብራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን አስመልክቶ በቂ መረጃ የሚሰጥ ድረ ገጽ ማበልጸግ በዩኒቨርሲቲው ከተከናወኑ ተግባራት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ተመራማሪዎችና የአካዳሚክ ክፍሉ በፈጠሩት ጠንካራ ጥምረት የተከናወኑ ውጤታማ የምርምር ተግባራት የዓለም አቀፍ እይታ እንዲጨምር ማስቻሉን የገለጹት ተ/ባ ፕሮፌሰር በኃይሉ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በተከናወኑ ውጤታማ የምርምር ፕሮጀክቶች ከ4,500 የአፍሪካ ተወዳዳሪዎች መካከል አሸናፊ መሆን ተችሏል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲው በእንሰት ፕሮጀክት የ380,000 ዩሮ ግራንት በቅርቡ አሸናፊ መሆኑን የጠቆሙት ም/ፕሬዝደንቱ በዚህም የዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የትብብር ፕሮጀክቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንዲሁም የኅትመት ውጤቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡ የመሰል ተግባራት ሥራ በየጊዜው እያደገ መሄድና መጨመር የዩኒቨርሲቲውን ዓለም አቀፍ ዕይታን ከመጨመራቸው ባሻገር ተቋሙ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ያግዛሉ ብለዋል፡፡
የአውሮፓና የአፍሪካ ሕብረት፣ የጀርመኑ GIZ፣ የአማሪካን ልማት ተራድኦ ድርጅት፣ ክርስቲያን ኤይድ፣ ቤልጂየም ሀገር የሚገኙ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ አልባስተር ኢንተርናሽናል፣ የጆሞ ኬኔያታ የግብርና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ካንሳስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ከሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት