የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹RUNRES - The Rural-Urban Nexus፡ Establishing Nutrients Loop to Improve City Region Food System Resilience Project›› ምዕራፍ አንድ ማብቂያና ምዕራፍ ሁለት ማስጀመሪያ ውይይት ግንቦት 22/2016 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ቆሻሻን አሰባስቦ ወደ ሀብት በመቀየር ዘላቂ የሆነ የቆሻሻ አወጋገድና መልሶ መጠቀምን የሚያጎለብትና ሌሎችም ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙና የለውጥ መሠረት የሚጥሉ ሥራዎች በፕሮጅክቱ ሥር ባሉ ኢንርፕራይዞች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
የ‹‹RUNRES›› ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አባይነህ ፈይሶ በምዕራፍ አንድ የሙከራ ወቅት ከገቡት 14 የቢዝነስ ዕቅዶች ውስጥ ሦስት የሚሸጥ ምርት እና አራት የግብዓት አቅራቢዎች ማኅበር በአጠቃላይ ሰባት ጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት ሲደገፉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሥራ አስኪያጁ ሙዝን አድርቆ በመፍጨት ለኬክ፣ ለኩኪስ፣ ለገንፎና ለአጥሚት መጠቀም የሚያስችል የምግብ ማቀነባበሪያ እና የሰው ሽንትን ጨምሮ ማዘጋጃ ቤታዊ ቆሻሻን አክሞ ወደ ማዳበሪያ መቀየርና ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ከማኅበራቱ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በምዕራፍ ሁለት በምግብ ማቀነባበሪያ (Agro-processing) እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት (Compost) ዘርፎች ቴክኖሎጂዎችን በማሻገር የሚሠራ ሲሆን የኮምፖስት ቴክኖሎጂ በጋሞ ዞን ብርብር ከተማ ይጀመራል ብለዋል፡፡ ከተማንና ገጠርን በንጥረ ነገር ማስተሳሰር፣ ዘላቂ የገቢ ምንጭ ማስገኘት፣ ለሴቶችና ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እና ጽዱ አካባቢን መፍጠር የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማዎች መሆናቸውን አቶ አባይነህ ተናግረዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ከተማ ሕዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ጥሩነሽ ተስፋዬ በዩኒቨርሲቲው ‹‹RUNRES›› ፕሮጀክት በምዕራፍ አንድ የተሠሩና በምዕራፍ ሁለት ሊሠሩ የታቀዱ ሥራዎች ለሌሎችም ተሞክሮ እንደሚሆኑ ተናግረው የተፈጥሮ ማዳበሪያን ተጠቅሞ ከኬሚካል የጸዳ የፍራፍሬ ምርት ማምረትና በሀገር አቀፍ ደረጃ ማሳወቅ ብሎም ሌሎች አካባቢዎችም እንዲያመርቱ ማድረግ ትልቅ ግብዓት ነው ብለዋል፡፡ ሥራውን በሰፊው በመሥራት ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ማኅበራትን ማደራጀትና ቅርንጫፎችን ማስፋት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡
‹‹እኛን ነው ማየት የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ቀልዝ) ሥራ ማኅበር›› አባል አቶ ተስፋ አምላኩ እንደገለጹት ቀደም ሲል 15 ቀንና ሳምንት እየፈጀ በሰው ኃይል የሚሠራውን ሥራ በ15 ደቂቃ ውስጥ ለመሥራት የሚያስችል ማሽን በፕሮጀክቱ በኩል በማግኘታቸው ሥራው በቀላሉ እንዲከናወን ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ከቤት ጥራጊ፣ ተረፈ ምግብና በስባሽ ነገሮች የሚሠራው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአንድ ኪሎ ሰባት ሊትር ፈሳሽ መያዝ የሚችልና የመሬትን ለምነት የሚጠብቅ መሆኑን እንዲሁም ጥሩ የገበያ ትስስር እንዳላቸው አቶ ተስፋ ተናግረዋል፡፡ ከተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር መተዋወቃችን ዘላቂ የሆነ ሥራ በጋራ እንድንሠራና በሁለተኛው ምዕራፍ በሙሉ አቅማችን እንድንንቀሳቀስ አነሳስቶናልም ብለዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት