በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳውላ ካምፓስ በልዩ ልዩ መስኮች በቅድመና ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ያሠለጠናቸውን 303 ተማሪዎች ሰኔ 15/2017 ዓ/ም ለ8ኛ ጊዜ አስመርቋል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት 38 ዓመታት 84,897 ብቁ ምሩቃንን ለሀገር ማበርከት የቻለ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ገልጸው ተቋሙ በርካታ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የምርምርና ማኅበረሰብ ተኮር ተግባራትን እያከናወነም ይገኛል ብለዋል። አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን እየሠራ መሆኑንም በንግግራቸው ፕሬዝደንቱ አውስተዋል። ምሩቃን ነገሮች በየጊዜው በሚቀያየሩበት በዚህ ዘመን የሕይወት ዘመን ተማሪዎች በመሆን ዕውቀታቸውን በየጊዜው ወቅታዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አጽንዖት ሰጥተው የተናገሩት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ምሩቃን ለሙያቸው፣ ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ታማኝና ሠላም ወዳድ እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢ/ር ዳግማዊ አየለ ትምህርት ለሀገርና ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ተናግረዋል:: የዕለቱ ምሩቃን በት/ት ቆይታችሁ ያገኛችሁትን ዕውቀት ወደ ተግባር የምትቀይሩበት ምዕራፍ ላይ ደርሳችኋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ምሩቃን በመንግሥት መቀጠርን ብቻ ሳይሆን በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ ያገኛችሁትን ዕውቀትና ክሂሎት ተጠቅማችሁ ሥራ ፈጣሪ መሆን አለባችሁ ብለዋል።
በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የሳውላ ካምፓስ ኃላፊ አቶ ዘለቀ ዶሳ የሳውላ ካምፓስ በ2008 ዓ/ም 180 ተማሪዎችን ተቀብሎ በ4 ፕሮግራሞች ሥራ መጀመሩን አስታውሰው ካምፓሱ በ2017 የት/ት ዘመን 3189 ተማሪዎችን በ30 የትምህርት ፕሮግራሞች ሲያስተምር መቆቱን ተናግረዋል። ትምህርት ረዥም መጓዝ የሚፈልግ በርካታ ውጣ ውረድ ማሳለፍ የሚጠይቅ የመጨረሻ ፍሬው ግን ጣፋጭ መሆኑን የገለጹት አቶ ዘለቀ ምሩቃን በቀጣይ ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በታማኝነት የሚያለግሉ እንዲሆኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን (አሉምናይ) ማኅበር ፕሬዝደንት አቶ ኤርሚያስ ዓለሙ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ቦታ የደረሱ እና ትልልቅ ተቋማትና ፕሮጀክቶችን የሚመሩና ብቃታቸው የተመሰከረላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል። የዕለቱ ምሩቃን ከዛሬ ጀምሮ የዩኒቨርሲቲው አምባሳደሮች ናችሁ ያሉት አቶ ኤርሚያስ በምትሰማሩበት የሥራ መስክ ሁሉ በቅንነትና በታማኝነት ሀገራችሁንና ህዝባችሁን የምታገለግሉ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲያችሁን ስም የምታስጠሩ ሁኑ ሲሉ መክረዋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ከየኮሌጁ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ምሩቃን ልዩ ሽልማት እና የላቀ ውጤት በማስመዝገብ አንደኛ ለወጡ የወርቅ ሜዳሊያ ተበርክቷል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት