የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ከሳሃይ ሶላር አሶሼሽን ጋር በመተባበር በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በዳዳ ጤና ጣቢያ 5 ኪሎ ዋት የሚያመነጭ የሶላር ኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማት ግንቦት 4/2018 ዓ.ም በድምቀት አስመርቋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በምርቃቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሶዶ ክላስተር አስተባባሪና የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ተፈሪ አባተ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት / ኢንጂነር አብደላ ከማል፣ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ፣ የማኅበረሰብ ጉድኝትና የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ፣ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለን ጨምሮ ሌሎች የዩኒቨርሲቲ፣ የዞንና የክልል አመራሮች የሀገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት / ኢንጂነር አብደላ ከማል ባደረጉት ንግግር ዩኒቨርሲቲው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች የሶላር ኃይል መሠረተ ልማቶችን በመገንባት አገልግሎት ማስጀመሩን ገልጸዋል። ዛሬም ለዳዳ ቀበሌ ጤና ጣቢያ ማስፋፊያ የሚሆን የሶላር ኃይል ማመንጫ  መሰረት ልማት አጠናቆ ማስመረቁን ተናግረው፣ ተቋሙ በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ የሚያከናውነውን ተግባር ለወደፊቱም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ተፈሪ አባተ ባደረጉት ንግግር ከዚህ ቀደም የጤና ባለሙያዎች በእጅ ባትሪ አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር ተናግረው ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ በመቻሉ በራሳቸውና በክልሉ ሕዝብ ስም ለዩኒቨርሲቲው ምስጋና አቅርበዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው የዳዳ ጤና ጣቢያ ሙሉ የሕክምና አገልግሎት እንዳይሰጥ ካደረጉት ዋና ዋና ችግሮች አንዱ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት አለመኖር እንደነበር ተናግረው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ችግሩን  ተረድቶ ከረጅም ርቀት በመምጣት ይህን የመሰለ ፕሮጀክት ገንብቶ በማስረከቡ በጎፋ ሕዝብ ስም አመስግነዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብና የጤና ባለሙያዎች ንብረቱን በጥንቃቄ እንዲይዙም ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።

የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር / ያሊሾ ግርማ በበኩላቸው ማዕከሉ ከተቋቋመበት 2009 . ጀምሮ 25 የገጠር ጤና ጣቢያዎች እና 20 የገጠር ትምህርት ቤቶች በድምሩ 45 የሶላር ኃይል ፕሮጀክቶችን በማከናወን የማኅበረሰብ አገልግሎት ተግባሩን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል። በዕለቱ የተመረቀውና 5 ኪሎ ዋት በላይ የማመንጨት አቅም ያለው የሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን፣ ይህም በዳዳ ቀበሌ የሚገኙ ሦስት መንደሮችን ጨምሮ 15 ሺህ በላይ ግለሰቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

 ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

 አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

 የጥበብ ምንጭ /Spring of Wisdom

 የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ /ቤት