የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ በ2016 ዓ/ም የ12ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና አሰጣጥ፣ አስተዳደርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ጉዳዩ ከሚመልከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሰኔ 21/2016 ዓ/ም የውይይት መድረክ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በእንኳን ደኅና መጣችሁ ንግግራቸው እንደ ሀገር የትምህርት ተደራሽነትን ከማስፋት አንፃር አመርቂ ውጤት የተመዘገበ ቢሆንም ከትምህርት ጥራትና አግባብነት አኳያ ግን ትልቅ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የሚስተዋለውን ችግር ለመቅርፍ እንደ ሀገር የትምህርትና ሥልጠና ፍኖታ ካርታ ተዘጋጅቶ መጠነ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን በፈተና አሰጣጥና አስተዳደር ዙሪያ ባለፉት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ከዚህ አንፃር የሚጠቀሱ መሆናቸውን ዶ/ር ዳምጠው አውስተዋል፡፡ የ12 ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለሁለት ዓመታት በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱን ያወሱት ፕሬዝደንቱ የዕለቱ የውይይት መድረክ ለ3 ጊዜ የሚሰጠውን ፈተና ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ በበኩላቸው በትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ እንደ ሀገር ከገጠሙን ስብራቶች መካከል አንዱ በምዘና ሥርዓታችን ሲስተዋል የቆየው ችግር ዋነኛው ሲሆን ይህም እንደ ሀገር ብቃት የሌለው ዜጋ እንዲፈራ በማድረግ ዋጋ አስከፍሎናል ብለዋል፡፡ ጸጋዎቻችንን ወደ ዕድል በመቀየር እንደ ሀገር ብቃት ያለው ዜጋ ለማፍራት በትምህርቱ ሴክተር ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ የዕለቱ የውይይት መድረክም በክልሉ በሚገኙ 4 ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠውን የ12 ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና አሰጣጥን በተሳለጠ መንገድ ለማከናወን ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባትን ለመፍጠርና ከዚህ ቀደም የገጠሙ ችግሮችን ነቅሶ ለማውጣት እንዲሁም መፍትሔዎችን ጭምር አፍልቆ ተግባራዊ ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የመማር ማስተማርና ምዘና  ዘርፍ  ኃላፊ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ እንደገለጹት የ2016 ዓ/ም የ12 ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወትሮው በተለየ መንገድ በወረቀትና በበይነመረብ ይሰጣል፡፡ እንደ ኃላፊው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 74,643 ተፈታኞች ዩኒቨርሲቲ ገብተው ፈተናውን የሚወስዱ ሲሆን 1,965 ተማሪዎች ደግሞ ፈተናውን በበይነመረብ ይወስዳሉ፡፡ ለፈተናው ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚገቡ የክልሉ ተፈታኞች መካከል 31,325 አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ 22,123 ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣ 10,812 ጂንካ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም 10,383 ዲላ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ መሆናቸውን አቶ ኢሳያስ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ በክልል ደረጃ የተዘጋጀ የፈተና አሰጣጥና አስተዳደር ማስፈፃሚያ እንዲሁም የጸጥታና ደኅንነት የሥራ እቅዶችን የያዙ ሁለት ሰነዶች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በውይይት መድረኩ የአርባ ምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ጂንካና ዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንቶች፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ የጸጥታና ደኅንነትና የፖሊስ ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች፣ የዞን ትምህርት መምሪያ፣ ጸጥታና ደኅንነት፣ ፓሊስ ኃላፊዎች እንዲሁም የመምህራን ማኅበር ተወካዮችና ሌሎች ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት