አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ“SIFA/Skills Initiative for Africa-Funding Window III” በሙከራ የተረጋገጡ የእንሰት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለሴቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በቀረጸው ፕሮጀክት አሸናፊ በመሆን ከአፍሪካ ኅብረት የልማት ኤጀንሲ(African Union Development Agency/AUDA-NEPAD) ጋር ነሐሴ 15/2016 ዓ/ም በአዲስ አበባ አፍሪካ ኅብረት አዳራሽ የጋራ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ስምምነቱን ተቋሞቻቸውን ወክለው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ተባባሪ ፕ/ር በኃይሉ መርደኪዮስ እና የኔፓድ “NEPAD” ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ናርዶስ በቀለ ተፈራርመዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ተባባሪ ፕ/ር በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በምርምር ተደግፎ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች መካከል የእንሰት ምርትና አመራረትን ለማዘመን የሚሠራቸው ፕሮጀክቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የእንሰት ቴክኖሎጂዎችን ፈጥሮ የማስፋፋት ሂደቱን የሚያግዙ አጋሮችን ሲያፈላልግ መቆየቱን የጠቀሱት ም/ፕሬዝደንቱ ይህ ፕሮጀክት ዕቅዱን ከግብ በማድረስ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሎም የእንሰት ዘመናዊ የአመራረት ሂደቶችን በሌሎች አካባቢዎችም በሰፊው ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ነው ብለዋል።
እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ፕሮጀክቱ በገምጋሚዎቹ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነትን ያገኘ መሆኑ የተቋሙንና የተመራማሪዎቹን አቅምና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳይ ነው፡፡ ይህም ለቀጣይ የጋራ ሥራዎች መሠረት የሚጥልና ተአማኒነትን የሚፈጥር ነው ያሉት ተባባሪ ፕ/ር በኃይሉ በመሆኑም በትልቅ ትኩረትና ኃላፊነት እንሠራለን ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱን ለማሸነፍ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ሁሉ በማመስገን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማእከል ዳይሬክተርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ‹‹ሉሲ እንሰት›› የግል ካምፓኒ እና አርባ ምንጭ ፖሊቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት በትብብር የሚተገበር ሲሆን የ18 ወራት ቆይታ ይኖረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ሲዳማ ክልሎች የእንሰት ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋትና አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን በመፍጠር 1,500 ያህል ሥራ አጥ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ዶ/ር ወንድወሰን ተናግረዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባዮቴክኖሎጂ ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አባል ዶ/ር አዲሱ ፍቃዱ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም የእንሰት ማምረትና ማብላላት ሂደትን የሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር በሙከራ ደረጃ አቅርቦ አመርቂ ውጤት ማሳየቱንና ቴክኖሎጂዎቹ የፈጠራ ባለቤትነት ማረጋገጫ ማግኘታቸውን አስታውሰው ይህ ፕሮጀክት ቴክኖሎጂዎቹን በሦስቱ እንሰት አብቃይ ክልሎች በሰፊው በማሰራጨት ለበርካታ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎችም አካላት የሥራ ዕድልን የሚፈጥርና የሴቶችን ከባድ የሥራ ጫና በማስቀረት ረገድ ከፍተኘ ሚና ያለው ነው ብለዋል፡፡
እንደ ዶ/ር አዲሱ ገለጻ በ3 ክልሎች 12 ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም የእንሰት ማቀናበሪያ ማሽኖችን ማምረት፣ የእንሰት ምግቦችን ማዘጋጀት እና ከእንሰት ተረፈ ምርት ጌጣጌጦችና ሌሎች ቁሳቁሶችን ማምረት የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማዎች ሲሆኑ ተጠቃሚዎችን መለየት፣ ፍላጎትና አቅርቦት ጋር የተያያዙ የገበያ ጥናቶችን ማካሄድ፣ ለሥራው አስፈላጊ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ የእንሰት ቴክኖሎጂዎችን አስመልክቶ በማኅበራዊ ሚዲያና ሌሎች አማራጮች ግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም ለኢንተርፕራይዞች መነሻ ግብዓቶችን ማቅረብ፣ ለምርቶቻቸው የገበያ ትስስር መፍጠር እና ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ ዝርዝር ተግባራት ናቸው፡፡
ፕሮጀክቱ በሲዳማ፣ በደቡብ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በተለያዩ የፌዴራል እና የክልል ተቋማት የጋራ ትብብር የሚተገበር ሲሆን የተገኘው ፈንድም በአሁናዊ ምንዛሪ ከ45.4 ሚሊየን ብር በላይ ነው፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት