የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ ፈጠራና ልማት ማበልጸጊያ ማዕከል ‹‹SNV/RAYEE/›› ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር ሲያካሂዱት የቆዩት 2ኛ ዙር የአርባ ምንጭ ከተማ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ውድድር ማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት ጥቅምት 22/2017 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት በኃይሉ መርደኪዮስ ተ/ባ ፕሮፌሰር እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ሀገራዊ ሥራዎችን ከማገዝ አንጻር ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን ማፍራትና የፋይንስ ድጋፍ የሚያገኙበትን ሥርዓት መፍጠር ላይ ያተኮሩ ተግባርትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ም/ፕሬዝደንቱ በውድድሩ ለተሳተፉ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ባስተላለፉት መልእክት ወጣቶቹ ተደጋግፎና ተያይዞ የማደግ ባህልን እንዲሁም ተሞክሯቸውን ለሌሎች የማካፈል ልማድን ማዳበር እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራና ልማት ማበልጸጊያ ማዕከል የሥልጠና ክፍል ኃላፊ መ/ር አበበ ዘየደ በበኩላቸው ማዕከሉ በቢዝነስ ሃሳብ፣ በቢዝነስ ፕላን አዘገጃጀትና አቀራረብ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥልጠናዎችን ለጀማሪና በሥራ ላይ ለሚገኙ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ጀማሪ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ማበረታታትና መደገፍ ዘላቂነት ያለው የሥራ ፈጠራ ሥርዓተ ምኅዳር ለመፍጠር ቁልፍ ሚና እንዳለውም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ የ‹‹SNV/RAYEE/›› አስተባባሪ አቶ አብነት ጴጥሮስ እንደተናገሩት ‹‹SNV/RAYEE/›› በኔዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር ያለ እና አስቀድሞ በበጎ ፈቃደኞች ስምሪት የተጀመረ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው። እንደ አስተባባሪው ገላጻ ድርጅቱ በግብርና፣ ኢነርጂ እንዲሁም በውኃ ልማትና አካባቢ ንጽሕና ላይ ትኩረት በመስጠት በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ከላይ በተጠቀሱት መስኮች ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ማበረታታትና መደገፍ ድርጅቱ በትኩረት ከሚሠራባቸው መስኮች መካከል አንዱ እንደሆነም አቶ አብነት ጠቁመዋል፡፡

የዶሮ ጫጩት መፈልፈያ ማሽን እና የዶሮ ኩስን አድርቆ ለእንስሳት መኖ አገልግሎት መስጠትን ትኩረት ባደረጉ የቢዝነስ ሃሳቦች ተወዳድረው የ100,000 እና የ80,000 ብር አሸናፊ የሆኑት ወጣት በኃይሉ ዳንኤል እና ወጣት ፋሲካ ደስታ ከዩኒቨርሲቲውና ከድርጅቱ ያገኙት የሥልጠናና የገንዘብ ሽልማት ሃሳባቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩና በኢኮኖሚ ደረጃም ይበለጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያገዛቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በማጠቃለያ ሥነ ሥርዓቱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ‹‹SNV/RAYEE/›› ጋር የፈጠሩት ጠንካራ ትስስር ጀማሪ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን በፋይናንስ ከመደገፍና ምቹ የገበያ ትስስር ከመፍጠር አንጻር የላቀ አስተዋጽዖ ማበርከቱ ተመላክቷል፡፡  


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት