አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን በአስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ እየሠራ ሲሆን ከሥራዎቹ አንዱ የሆነውን የተቋሙን ስትራቴጂክ ዕቅድ ክለሳ አከናውኖ ዛሬ ታኅሣሥ 23/2017 ዓ/ም በተከለሰው ረቂቅ ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ የውስጥ ግምገማ አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ተ/ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ስትራቴጂክ ዕቅዱን በመከለስ ሒደት ውስጥ ጊዜያቸውንና ዕውቀታቸውን ሳይሰስቱ ለሠሩ ኮሚቴዎች ምስጋናቸውን በዩኒቨርሲቲው ስም አቅርበዋል፡፡ በውይይቱ ስትራቴጂክ ዕቅዱን ይበልጥ ለማሻሻል የሚረዱ ገንቢ አስተያየቶች የተሰጡ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቱ ኮሚቴው የተሰጡ አስተያየቶችን አካቶ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡ ስትራቴጂክ ዕቅዱን አሁን ካለበት ይበልጥ ከዩኒቨርሲቲው የመስክና የልኅቀት ማዕከል ልየታ፣ ራስ ገዝ ከመሆን እንዲሁም ከሪፎርም አጀንዳዎች አኳያ በደንብ መቃኘት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ በፍጥነት መሮጥና የሚታይ ለውጥ ማስመዝገብ ያለብን ጊዜ ላይ ነን ያሉት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ የዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ተመሥርተው ሁሉም ኢንስቲትዩቶች፣ ኮሌጆችና ት/ቤቶች የራሳቸውን ስትራቴጂክ ዕቅድ ማዘጋጀትና መከለስ እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ትብብር ተ/ም/ፕሬዝደንትና የስትራቴጂክ ዕቅድ ክለሳ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የስትራቴጂክ ዕቅድ አሠራሩንና ሥራው የተመራበትን መንገድ አስመልክቶ ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን መወሰኑ፣ ለዩኒቨርሲቲው የተሰጡ የመስክና የልኅቀት ማዕከል ዘርፎች ልየታና የተለያዩ የሪፎርም አጀንዳዎች በመኖራቸው የዩኒቨርሲቲውን ስትራቴጂክ ዕቅድ መከለስ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡ ከዋናው ዐቢይ ኮሚቴ ባሻገር ሌሎች የየዘርፍ ባለሙያዎችን የያዙ ሰባት ንዑሳን ኮሚቴዎች ተደራጅተው ስትራቴጂክ ዕቅዱን ማዘጋጀታቸውን የገለጹት ዶ/ር ተክሉ ስትራቴጂክ ዕቅዱ ከመዘጋጀቱ በፊት የተለያዩ ፖሊሲዎችን፣ መመሪያዎችንና ስትራቴጂዎችን የመፈተሽ እንዲሁም እንደ ተቋም ያሉ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን፣ መልካም አጋጣሚዎችንና ችግሮችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የመተንተን ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝ አስተዳደር ፕሮጀክት ማኔጀር ዶ/ር ቤታ ፀማቶ የስትራቴጂክ ዕቅዱን ዝርዝር ይዘት አስመልክቶ ባቀረቡት ገለጻ የተከለሰው ስትራቴጂክ ዕቅድ የተቋሙን ተልእኮና የሪፎርም አጀንዳዎች በተከተለ መልኩ 8 ስትራቴጂካዊ ግቦችን ወይም ጭብጦችንና አርባ አንድ ዓላማዎችን የያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ስትራቴጂክ ዕቅዱን ለማዘጋጀት የራስ ገዝ አዋጅን ጨምሮ ኮሚቴው አሥራ ስድስት ፖሊሲዎችን፣ አዋጆችን፣ ደንብና መመሪያዎችን እና ሌሎች ዶክሜንቶችን መመልከቱን አውስተዋል፡፡ በቀጣይ የተከለሰው ስትራቴጂክ ዕቅድ ማስተካከያዎች ተደርገውበት ስትራቴጂክ ዕቅዶችን ለመገምገም በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለተቋቋመው አማካሪ ቦርድ የሚቀርብ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የቀረቡ ገለጻዎችን ተከትሎ ተሳታፊዎች በተከለሰው ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ በርካታ አስተያየቶችንና ጥያቄዎች አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት