የ3ኛ ዓመት የፋርማሲ ተማሪ ለሆነችው ተማሪ ሜሮን ካፒታ ሕክምና በተለያዩ መንገዶች ያሰባሰበውን 416,927.45 ብር (አራት መቶ ዐሥራ ስድስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሃያ ሰባት ብር ከ45 ሳንቲም) ድጋፍ ማድረጉን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኅብረት ጥቅምት 01/2017 ዓ/ም አስታውቋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ድጋፉ የሁሉም ካምፓስ ተማሪዎች የሁለት ቀናት የቁርስ ወጪያቸውን ተስማምተው በመስጠት ለተማሪዋ ሕክምና እንዲውል 192,693.45 ብር እንዲሁም 224,234 ብር ያህሉ ደግሞ በተለያዩ መንገዶች ያሰባሰቡት መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ሶፎንያስ ፈንቴ ተናግሯል፡፡

የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደቱ መስከረም 24/2017 ዓ/ም ‹‹ለወገን ደራሽ ወገን ነው›› በሚል መሪ ቃል የተጀመረ መሆኑን የገለጸው ፕሬዝደንቱ በከተማውና በዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች ውኃ በመሸጥ፣ ጫማ በመጥረግ እንዲሁም በከተማ መግቢያና መውጫ በሮች ላይ ከአሽከርካሪዎች፣ ከተሳፋሪዎችና ከነዋሪዎች ገንዘብ በመሰብሰብ ድጋፉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የኅብረቱ ፕሬዝደንት ሥራው በተሳካ ሁኔታ እንዲሠራ ላደረጉ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና አጠቃላይ ማኅበረሰብ፣ ለአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች፣ ለአርባ ምንጭ ከተማ ትራፊክ ፖሊሶች እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ላሳዩት ላቅ ያለ በጎነት በኅብረቱ ስም ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

ተማሪ ሜሮን ካፒታ ዋልጬ ባጋጠማት የኩላሊት ሕመም በሕክምና ስትረዳ ጉዳዩ ከአቅም በላይ በመሆኑ ወደ ውጭ ሀገር (ሕንድ) ተልካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ እንዲደረግላት በሐኪሞች ተወስኖ ድጋፍ ሲሰበሰብላት የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡:

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት