በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ የሚገኘው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት አመራርና መምህራን ሀገር አቀፍ ልዩ ሥልጠና በተጠናከረ ሁኔታ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን የሥልጠና ሂደቱን ተመልክተዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታዋ በሥልጠና ክፍሎች በመዘዋወር ሠልጣኞችን ሲያበረታቱ እንደተናገሩት ሥልጠናው የመምህራንን የማስተማር ዕውቀትና ክሂሎት የሚያዳብር ሲሆን ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራት ከማሳደግ ተልእኮ አኳያ በርካታ ለውጦችን በሀገር ደረጃ እያከናወነ እንደሚገኝና ይህም ልዩ ሥልጠና የዚሁ ሥራ አካል ነው፡፡ ትውልድን የማሻገር ኃላፊነትና መስዋዕትነት መክፈል የሁላችንም ድርሻ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ሠልጣኞች ሥልጠናውን በትኩረት እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጂ ዲንና የጫሞ ካምፓስ ኃላፊ ዶ/ር መስፍን መንዛ እንደገለጹት 1,800 የሚሆኑ ተሳታፊዎች በ68 ክፍሎች ተከፋፍለው የመምህራን ሙያ ማሻሻያ ሥልጠናውን በተገቢው ሁኔታ እየወሰዱ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የ“STEM DESK” የፊዚክስ ባለሙያና የሥልጠናው አስተባባሪ አቶ ደሴ መለሰ እንደተናገሩት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሁሉም መምህራን ሥልጠናውን መውሰድ የሚገባቸው ቢሆንም በቅድሚያ ለሒሳብ፣ ለሳይንስና ለቋንቋ ትምህርቶች ትኩረት በመስጠት በሁሉም 28 ዩኒቨርሲቲዎች ሥልጠናው እየተሰጠ ነው፡፡ ሥልጠናው በአዲሱ ፍኖተ ካርታ መሠረት በተዘጋጁ ሞጅሎች መሠረት በዩኒቨርሲቲ መምህራን አማካኝነት እየተሰጠ እንደሚገኝ አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና አሠልጣኝ ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ እንደገለጹት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት አመራርና መምህራን አቅም ግንባታ ልዩ ሥልጠና በትምህርት ሚኒስቴር በተዘጋጀው መርሃ ግብር መሠረት በጥሩ ሁኔታ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ እንደ አሠልጣኙ ሥልጠናው የመማር ማስተማር አካሄድን በተግባርና በቴክኖሎጂ ማስደገፍ ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን የተማሪዎች የመማር ፍላጎትንና ተነሳሽነትን ከፍ ለማድረግ መምህራንን ማብቃት አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን ግብ ለማሳካት የተዘጋጀ ነው፡፡
በተመሳሳይም የዩኒቨርሲቲው መምህርና አሠልጣኝ ዶ/ር ቤታ ጸማቶ ሠልጣኞች ሥልጠናውን በልዩ ትኩረት እየተከታተሉ እንደሚገኙ፣ በልዩ መመሰጥ እርስ በእርስ እየተወያዩ እንደሚማማሩና ከሥልጠና በኋላ በሚኖረው ምዘና እያንዳንዳቸው ከ90 ፐርሰንት በላይ ውጤት ለማስመዝገብ ግብ አስቀምጠው እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት