አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚሰጠው የመምህራንና የር/መምህራን ልዩ የክረምት ሥልጠና ከጋሞ ዞንና አጎራባች የ2 ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ ሠልጣኞች ሐምሌ 22/2016 ዓ/ም ገለጻ ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በኦንላይን በቀጥታ ባስተላለፉት የመክፈቻ መልዕክት እንደገለጹት መምህራን የታሪክ ተቆርቋሪዎች፣ አንባቢያን፣ ታሪክን የሚያስተላልፉና የሀገር ተስፋ ናቸው፡፡ የሀገራችንን የብዙ ዘመናት ችግሮችን ለመቅረፍ ትውልዱ በመልካም ሥነ ምግባር ተቀርጾ ሀገሩን እንዲያጸና የማድረግ ትልቁ ሚና የመምህራን መሆኑን ዶ/ር ዐቢይ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ አንጻር መምህራንና ርዕሰ መምህራን ትውልዱን ለመቅረጽ በሚያደርጉት ሂደት ትውልዱ ሀገር ወዳድና አገልጋይ እንዲሆን፣ ከእርዳታና ልመና መንፈስ ወጥቶ ለአዳዲስ የፈጠራና ቴክኖሎጂ ሃሳቦች ትኩረት አንዲሰጥ ከማድረግ አንጻር ልዩ ሥልጠናው መምህራን በሚያስተምሩት የትምህርት ዓይነት ላይ የተሻለ ዕውቀት እንዲኖራቸው አቅም የሚያጎለብት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ውጤታማና ጥራቱን የጠበቀ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲኖር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን ልዩ የክረምት ሥልጠና ገለጻው በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መከፈቱ የሥልጠናውን ክብደት ያሳያል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ሠልጣኞቹ በሚኖራቸው ቆይታ ሙሉ ጊዜና ትኩረታቸውን መስጠት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት የትምህርት ጥራትን በተመለከተ የተለያዩ ለውጦች እንዳሉ ጠቅሰው ሥልጠናው በዋናነት መምህራን በሙያው መስክ፣ በሥነ ትምህርትና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ እንደሚሰጥና እንደ ሀገር የሚታየውን የትምህርት ጥራት ችግር ለማሻሻል እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሥነ ትምህርትና ሥነ ባህርይ ት/ቤት ዲን እና የሥልጠናው አስተባባሪ አቶ አንለይ ብርሃኑ እንደገለጹት ሥልጠናው የመምህራንን የመማር ማስተማር ዕውቀትና ክሂሎት የሚያዳብር ሲሆን በሀገር ደረጃ የወደቀውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍ የተወሰደው የመምህራንን አቅም ማጎልበት አስፈላጊ ስለሆነ ትምህርት ሚኒስቴር በክረምት መርሃ ግብር ልዩ ሥልጠና ለመስጠት ወስኗል፡፡

እንደ አቶ አንለይ የሥልጠናው ዋና ዓላማ መምህራን በሚያስተምሩት የትምህርት ዓይነት አቅም ማጎልበት፣ የተከታታይ ሙያ ማሻሻያ ሥርዓትን ማጠናከር እንዲሁም የተማሪዎች የመማር ፍላጎትና ውጤት ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ 52,300 የ2 ደረጃ ት/ቤት መምህራን እና 8,070 የት/ቤት አመራሮች በጠቅላላው 60,370 ሠልጣኞች በተመረጡ 28 ዩኒቨርሲቲዎች ሥልጠናውን የሚወስዱ ሲሆን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 2,059 ሠልጣኞች እንደሚሠለጥኑ ዲኑ ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞች በሒሳብ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ፊዚክስ፣ እንግሊዝኛ ቋንቋ፣ የትምህርት አመራርነት፣ ሥነ ትምህርት፣ የማስተማሪያ ሥነ ዘዴ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እና የሥነ ልቦና ትምህርትና የአመራርነት ክሂሎት የሚሠለጥኑ ሲሆን ከሥልጠናው በፊት ቅድመ ምዘናና ከሥልጠናው በኋላ ድኅረ ምዘና የሚሰጥ ይሆናል፡፡ የምዘና ውጤታቸው ከ70 በመቶ በላይ የሆኑ የምስክር ወረቀት የሚያገኙ መሆኑ በገለጻው ተጠቁሟል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት