ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዛራ የሳይንስ ባችለር ዲግሪ በባዮሎጂ በ1997 ዓ.ም፣ የሳይንስ ማስተርስ ዲግሪ በባዮሜዲካል ሳይንስ በ2001 ዓ.ም እና የዶክትሬት ዲግሪ በትሮፒካል እና ተላላፊ በሽታዎች ትምህርት ዘርፍ በ2008 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡
በቻይና ሄናን ግብርና ዩኒቨርሲቲ በዞኖቲክ በሽታዎች ዓለም አቀፍ የጋራ ምርምር ላቦራቶሪ ከፍተኛ ሞሌኩላር ሥልጠና ለሦስት ወራት የወሰዱት ዶ/ር ተክሉ ወደ እስራኤል ሀገር በመጓዝም በአሪል ዩኒቨርሲቲ እና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መካከል የኢንተር-ዩኒቨርሲቲ ትብብር መሥርተዋል፡፡ በአፍሪካ ሀገራትም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ተክሉ በአሁኑ ጊዜ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ ትምህርት ክፍል የትሮፒካል እና ተላላፊ በሽታዎች ተባባሪ ፕሮፌሰር በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
ዶ/ር ተክሉ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ከተቀጠሩበት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በመማር ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማኅበረሰብ አገልግሎት በተማሩበት የሙያ መስክ ተቋሙንና በዙሪያው ያለውን ማኅበረሰብ አገልግለዋል፤ በማገልገል ላይም ይገኛሉ፡፡ በመማር ማስተማሩ ዘርፍ በሙያ መስካቸው ለቅድመ ምረቃና ድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ኮርሶችን በመስጠት እንዲሁም በጥናትና ምርምሩም ዘርፍ በልዩ ልዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ምርምሮችን በመሥራት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በዚህም 35 የምርምር ጽሑፎችን በስመጥር ዓለም ዓቀፍ ጆርናሎች ላይ ማሳተም ችለዋል፤ እንዲሁም የ‹‹OMO International journal of Science›› ተባባሪ ኤዲተር በመሆን እ.ኤ.አ ከ2019 እስከ 2024 አገልግለዋል፡፡
ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ አዳዲስ ሥርዓተ ትምህርቶች ሲቀረጹ በመገምገም እንዲሁም ከሰባ የሚበልጡ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን የምርምር ሥራ በመገምገምና በመፈተን ሙያዊና ሀገራዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል፤ በመወጣትም ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አርባ አምስት የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን የምርምር ሥራ በማማከር ያስመረቁት ዶ/ር ተክሉ በአሁኑ ወቅት የስምንት የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን የምርምር ሥራ በማማከር ላይ ይገኛሉ፡፡
ዶ/ር ተክሉ ከመማር ማስተማርና ከምርምር ሥራዎች ጎን ለጎን ዩኒቨርሲቲውን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎችም አገልግለዋል፡፡ በዚህም ከየካቲት 2002 እስከ መስከረም 2004 ዓ.ም የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ተቋማዊ ጥራት ማጎልበቻ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ ከሐምሌ 2008 እስከ ሚያዝያ 2009 ዓ.ም የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ልዩ ረዳት፣ ከሚያዝያ 2009 እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ ከሐምሌ 2016 እስከ ኅዳር 2017 ዓ.ም የድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፡፡ በተጨማሪም ከጳጉሜ 2008 እስከ ሚያዝያ 2009 ዓ.ም የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ እንዲሁም ከየካቲት 2009 እስከ ኅዳር 2010 ዓ.ም የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ በመሆን የተሰጣቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና በትጋት ተወጥተዋል፡፡
ዶ/ር ተክሉ በተለያዩ ተቋማት የቦርድ ሰብሳቢ እና አባል በመሆንም አገልግለዋል፡፡ በዚህም ከመስከረም 2010 እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤቶች ቦርድ ሰብሳቢ፣ ከየካቲት 2014 እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም የጋሞ ባይራ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቦርድ አባል እንዲሁም የአርባ ምንጭ አቡነ ሰላማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል፤ በማገልገል ላይም ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተቋሙ ውስጥ ለተለያዩ ልዩ ተልእኮዎች በሚቋቋሙ ኮሚቴዎች ሰብሳቢና አባል በመሆን የሠሩት ዶ/ር ተክሉ በአሁኑ ወቅት የዩኒቨርሲቲውን የአስር ዓመት ስራቴጂክ ዕቅድ ክለሳ ኮሚቴ በሰብሳቢነት እየመሩ ይገኛሉ፡፡
ዶ/ር ተክሉ በእስከ አሁን ቆይታቸው በመማር ማስተማር፣ በምርምር እንዲሁም በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ዩኒቨርሲቲውን በትጋት ሲያገለግሉ መቆየታቻውን ታሳቢ በማድረግ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ከታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ሆነው በውክልና እንዲያገለግሉ መድቧቸዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት