የፌዴራል ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ልኡካን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት በዕውቅና (Accreditation)፣ የኢንደስትሪ ትስስር፣ የልማት ሥራዎች እና የትብብር ሥራዎች ዙሪያ ውይይትና ምልከታ አካሂደዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በሚኒስቴሩ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት ክትትልና ድጋፍ ዴስክ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዓለማየሁ ፍሥሃ ውይይትና ምልከታው የተጠሪ ተቋማቱን አገልግሎት ማስተዋወቅ እና ከዕውቅና አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የዩኒቨርሲቲው ቤተሙከራዎች ያሉበትን ይዞታ መመልከትን ዓላማ አድርጎ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ አቶ ዓለማየሁ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከአምራች ኢንደስትሪዎች ጋር የሚራቸውን ሥራዎች እና በሥሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማት የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የላቦራቶሪ አክሬዲቴሽን አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ሥነ ልክ ኢንስቲትዩት የሚሰጡትን አገልግሎት አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል፡፡ 

የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት ክትትል ዘርፍ ባለሙያ አቶ ደጀኔ ከበደ ዩኒቨርሲቲው ከጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት ጋር ጠንካራ ትስስር በመፍጠር የሚሰጡትን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ዐውቆ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ደ/ር ኤፍሬም ጌታሁን በዩኒቨርሲቲው በ2017 ዓ/ም 36 የላቦራቶሪ ባለሙያዎች የISO/IEC 17025:2017 ሥልጠና ወስደው የዕውቅና ምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን አስታውሰው  በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ካምፓሶች ያሉ ቤተ ሙከራዎች ዕውቅና እንዲያገኙ የዶክመንት ዝግጅትና ዳግም የማደራጀት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ውይይትና ምልከታውም ዩኒቨርሲቲው የጀመራቸው ሥራዎች ከስኬት እንዲደርሱ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ለመሆን እየሠራ እንደመሆኑ የጥራት ተቋማቱን አስመልከቶ የተሰጠው ገለጻ የቤተ ሙከራ፣ ግንባታና የውኃ ሥራዎች እንደ ማኅበረሰብ ጉድኝት ብቻ ሳይሆን በገቢ ማስገኛነት ለመሥራትም ጭምር የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት