አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጋሞ ዞንና አጎራባች የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተወጣጡ መምህራንና የት/ቤት አመራር አካላት ልዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለሚያሰለጥኑ መምህራን የአሠልጣኞች ሥልጠና ከሐምሌ 17 - 19/2016 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመልካም ሥነ ምግባር የታነጹና ውጤታማ የማስተማር ሥነ ዘዴን የሚከተሉ መምህራንን ለማፍራት በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት አሠልጣኞች በሥራ ዓለም ያካበቱትን ዕውቀትና ክሂሎት በማካፈል የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው ሥልጠናው በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ልዩ ትኩረት የተሰጠውና በሀገር ደረጃ የገጠመውን የትምህርት ስብራት ለመጠገን ከፍተኛ አቅም ያለው በመሆኑ ለሥልጠናው ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሳይንስ ተፈጥሮን መረዳት ከመሆኑ ባሻገር ለአንድ ሀገር እድገት ሚናው የጎላ ነው ያሉት የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ የሳይንስ ትምህርት ዘርፎች ትኩረት በማጣታቸው ምክንያት ተማሪዎች ትምህርቱን እንዲጠሉት የዳረገ ሲሆን አሁን ላይ በሀገር ደረጃ የትምህርት ጥራትን ለማምጣትና ብቁ መምህራንን ለማፍራት ሳይንስና መሰል የትምህርት መስኮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥልጠናዎች መዘጋጀታቸው የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሥነ ትምህርትና ሥነ ባህርይ ት/ቤት ዲን መ/ር አንለይ ብርሃኑ እንደገለጹት ሥልጠናው የመምህራንን የማስተማር ዕውቀትና ክሂሎት ማሻሻል፣ የተከታታይ ሙያ ማሻሻያ ሥርዓትን ማጎልበት እንዲሁም የተማሪዎችን የመማር ፍላጎትና ውጤት ማሻሻልን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ እንደ ዲኑ 2,059 የ2ኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራንና የት/ቤት አመራር አካላትን ለማሠልጠን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና ከአርባ ምንጭ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የተወጣጡ 93 አሠልጣኝ መምህራን ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሠልጣኞች ከሥልጠናው በፊትና በኋላ ምዘና የሚወስዱ ሲሆን የምዘና ውጤታቸው ከ70 በመቶ በላይ ለሆኑ ሠልጣኞች ብቻ የምስክር ወረቀት የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡ በተጨማሪም በምዘናው ያለፉ መምህራንና የት/ቤት አመራር አካላት የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን የሚያገኙበት ሥርዓት በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የሚዘረጋ ሲሆን በአንጻሩ የምዘና ሂደቱን ያላለፉ ሠልጣኞች መሰል የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን በድጋሚ የሚወስዱ ይሆናል፡፡
በሒሳብ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ፊዚክስ፣ እንግሊዝኛ ቋንቋ፣ የትምህርት አመራርነት፣ የማስተማሪያ ሥነ ዘዴ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲሁም የሥነ ልቦና ትምህርትና የአመራርነት ክሂሎት ላይ ለ2ኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራንና ለት/ቤት አመራር አካላት ከሐምሌ 22 - ነሐሴ 16 /2016 ዓ/ም ሥልጠና ለመስጠት መታቀዱም ተገልጿል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት