በአርባ ምንጭ  ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለሳውላ ከተማ የሳምንት መጨረሻ  የኅብረተሰብ ጤና የ2ኛ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማሳተፍ በሳውላ ከተማ በጉረዴ ቀጠና የተሰራ ከ200 በላይ አባወራዎችን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ የሚያደርግ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ሰኔ 28/2017 ዓ/ም ተመርቋል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ፕሮጀክቱ ኅብረተሰቡን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለኅብረተሰቡ ጤና መሻሻል የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ተጠቁሟል።

በዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ዩኒቨርሲቲው ዘርፈ ብዙ የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው ተመራቂ ተማሪዎቹ የስሩት ፕሮጀክት በሌሎች የትምህርት መስኮችም መቀጠል ያለበትና ማኀበረሰብን በማሳተፍ ለሚሰሩ የማኀበረሰብ ጉድኝት ሥራዎች ምሳሌ የሚሆን መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣይ መሰል የልማት ተግባራት ተደራሸነታቸውን በሌሎች አካባቢዎችም ጭምር የማስፋፋት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ለዚህም ሁሉም በቅንጅትና በትብብር እንዲሰራ አጽንዖት ሰጥተዋል።

የሳውላ ካምፓስ ኃላፊ አቶ ዘለቀ ዶሳ ካምፓሱ ከምሥረታው አንስቶ በተለይ በማኅበረሰብ አገልግሎት በኩል የትምህርት ዕድል የአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆንና ለአካባቢው ማኀበረሰብ ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል። መሰል የማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች በተናጠልና በቅንጅት እንደሚሠሩና የማኀበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረቶች እንደሚጠናከሩ ጠቁመዋል።

የኮሌጁ የማኅበረሰብ አቀፍ ትምህርት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ መ/ር ፍርዳወቅ ጌታሁን  በዩኒቨርሲቲው  ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሳውላ  ከተማ  በሳምንት መጨረሻ መርሃ ግብር  በኅብረተሰብ  ጤና ትምህርት የ2ኛ ዲግሪ የሚከታተሉ ተማሪዎች ልማታዊ የቡድን ሥልጠና ፕሮግራምን /Developmental Team Training Program /DTTP/ መሠረት በማድረግ የተሰራ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው ዓላማው ተማሪዎች በሳይንሳዊ መንገድ የማኅበረሰቡን ችግር ከለዩ በኃላ የአካባቢውን ማኅበረሰብ እና የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር ለችግሩ ተገቢ ምላሽ መስጠት እንደሆነ ተናግረዋል።

የሳውላ ከተማ ውኃ አገልግሎት ኃላፊና የከተማው አስተዳደር ተወካይ ኢ/ር ኤልሳ ጣሊያን ፕሮጀክቱ የተሰራበት አካባቢ ከዋናው ከተማ ወጣ ያለና በርቀት እንደመገኘቱ ከንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት አንጻር ችግር ያለበት መሆኑን ገልጸው በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በኩል ፕሮጀክቱ በዚህ መልኩ እውን መሆን መቻሉ ማኅበረሰቡን በእጅጉ የሚጠቅም መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይም ማኀበረሰቡን ያሳተፉ መሰል የማኅበረሰብ ተኮር ልማታዊ ሥራዎች እንድጎለብቱ  ከባለድርሻ አካላት ጋር ጽ/ቤታቸው በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጉረዴ ቀጠና አስተዳደር አቶ አብራሃም ዞንባ በሰጡት አስተያየት የአካባቢው ማኅበረሰብ ለረዥም ዓመታት የንጹህ መጠጥ ውኃ ፍለጋ ረጅም መንገድ ይጓዝ እንደነበርና ለተጨማሪ ወጪዎችም ሲዳረግ መቆየቱን ተናግረዋል።  ይህ ፕሮጀክት በዚህ መልክ ተጠናቆ አገልግሎት መሰጠት መጀመሩ ትልቅ እፎይታ እንደፈጠረና በቀጠናው ነዋሪዎች ስም ለተማሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።

ተማሪ አቤነዘር ተክሉ ተማሪዎችን በመወከል ባስተላለፈው መልዕክት ፕሮጀክቱ በ17  የኀበረተሰብ ጤና የሳምንት መጨረሻ ተመራቂ ተማሪዎች የአካባቢውን ማኀበረሰብ አስተባብረው የሰሩት ሲሆን አጠቃላይ ከ150,000 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገበት መሆኑን ገልጿል።

‎በፕሮግራሙ ላይ የሳውላ ከተማ አስተዳደር፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮችና የአካባቢው ማኅበረሰብ የተገኙ ሲሆን ለፕሮጀክቱ መሳካት ልዩ ድጋፍና አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና አካላት የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል ።

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት