የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት በዩኒቨርሲቲው ክላስተር ሥር ከሚገኙ የኢንተርፕራይዝ ልማት መዋቅሮች፣ ከአካባቢው ኢንደስትሪዎች እና ከትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ጋር የንዑስ ቀጠናዊ ትስስር ፎረም የጋራ ውይይት ታኅሣሥ 26/2017 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

መድረኩ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት የቀሪ 6 ወራት መሪ ዕቅድ ላይ ውይይት ለማካሄድ የተዘጋጀ ነው፡፡

የምርምርና ትብብር ተ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የተቋምን ውጤታማነት ለማሳደግ መሰል የትስስርና የትብብር ፎረሞች አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲና በኢንደስትሪዎች መካከል የሚፈጠሩ ትብብሮች የፈጠራ ውጤቶችን ከማጎልበት፣ የሥራ ዕድል ከመፍጠር እንዲሁም የተሻለና ብቃት ያለው የሰው ኃይል ከማፍራት አንጻር የጎላ ሚና የሚያበረክቱ በመሆናቸው ትስስሩን ይበልጥ ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለጹት ፎረሙ እንደ ሀገር ተመሥርተው ወደ ተግባር እንዲገቡ ከተደረጉ አካባቢያዊ የትስስር ፎረሞች መካከል አንዱ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲው ክላስተር ሥር የሚገኙ የጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶና ባስኬቶ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መዋቅሮችና የማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ልማት ዘርፎች እና የአ/ምንጭ፣ ሳውላ፣ ካምባ፣ ካራት፣ ሰገን፣ ሰላም በር፣ ዋጫ፣ ገረሴ፣ ጋርዱላ፣ ላሃና ላሰካ ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት በፎረሙ ታቅፈው በጥምረት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ዶ/ር ቶሌራ ጠቁመዋል፡፡ በፎረሙ የኢንተርፕራይዞችን ብቃትና ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉና የኅብረተሰቡን ችግሮች በጥናትና ምርምር መፍታት የሚያስችሉ የትብብር ሥራዎች እንደሚሠሩም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት ም/ዲን እና የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንደስትሪ ኤክስቴሽን ዋና ሥራ ሂደት አቶ ወርቅነህ ሀ/ሚካኤል አሁን ላይ እንደ ሀገር ከዘርፉ ትልቅ ሥራ የሚጠበቅ በመሆኑ ፎረሙን በአዲስ አደረጃጀት ማጠናከርና ቴክኖሎጂን በማሻገር፣ የማኅበረሰብ ማማከር አገልግሎት በመስጠት፣ የአሠልጣኞችን አቅም በማጎልበት እና የቢዝነስ ሃሳቦችን በማሳደግ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ 


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት