‹‹Vita/RTI-Ethiopia›› የተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ለድንችና ሌሎች ዕፅዋት ምርምር የሚያግዙ ግማሽ ሚሊየን ብር ያህል ዋጋ ያላቸው የላቦራቶሪ ግብአቶችን ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ሐምሌ 24/2016 ዓ/ም ድጋፍ አድርጓል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ከበሽታ የጸዳ የድንች ዘር ለማግኘት የሚያስችሉ ለምርምርም የሚሆኑ ኬሚካሎች፣ ከበሽታ ነጻ የሆኑ የድንች ዘሮች ማራቢያ ማዕከል (Screen house)፣ የዕፅዋት ላቦራቶሪ ቁሳቁሶች፣ የዕቃ ማጽጃዎች፣ የባለሙያዎች የደንብ አልባሳትና ጫማዎች እንዲሁም ሌሎች ለዕፅዋት ዘር ማሻሻያ የሚሆኑ ግብአቶች በድርጅቱ በድጋፍ ከቀረቡ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ ከዚህ ቀደም ከተመራማሪዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በዕፅዋት ቲሹ ካልቸር ላይ ለመሥራት ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰው በዩኒቨርሲቲው የቲሹ ካልቸር ላቦራቶሪ በማደራጀት ከበሽታ የጸዳ የድንች ዘርን አሻሽሎ በማስፋፋት ሂደት ላይ ግብአቶችን በማቅረብና ባለሙያዎችን በማሠልጠን ግብረ ሠናይ ድርጅቱ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
የ‹‹Vita/RTI-Ethiopia›› ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ አስፋው መኩሪያ ድርጅታቸው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመሥራት ከተፈራረመ 10 ዓመት እንደሚሆን ገልጸው በቆይታቸውም ከመማር ማስተማር ጋር ተያይዞ ዩኒቨርሲቲውን በሥልጠናና በአቅም ግንባታ ሥራዎች ከመደገፍ ባለፈ በተለያዩ ዘርፎች የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን በትብብር ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ድርጅታቸው በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከእርሻ ምርምር ማዕከላት ጋር ለረዥም ዓመታት በዕፅዋት ዘርፍ ላይ ሲሠራ የቆየ ሲሆን ከበሽታ የጸዳ የድንች ዘር ማሻሻያ ላይ ያለውን ልምድ ወደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በማምጣት ዩኒቨርሲቲው በተለይ በድንች የዘር ማሻሻያ ላይ እያደረገ ላለው ምርምር እንዲረዳው የዕፅዋት ቲሹ ካልቸር ላቦራቶሪን ማጠናከር የሚያስችሉ ግብዓቶች ድጋፍ አድርጓል፡፡
በድርጅቱ የአርባ ምንጭ ተጠሪ አቶ ፀሐዩ ካሴ በበኩላቸው ድርጅታቸው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በጋሞ ዞን ድንች በስፋት እንዲመረት እየሠራ እንደሚገኝና በዚህም የድንች ዘሮች በየጊዜው እየተሻሻሉ እንዲሄዱ ድርጅታቸው እንደሚያበረታታ ተናግረዋል፡፡ አቶ ፀሐዩ ከበሽታ ነጻ የሆኑና የተሻሻሉ የድንች ዝርያዎች እንዲገኙ ዩኒቨርሲቲው እያደረገ ላለው ምርምር ላቦራቶሪውን ለማጠናከር ድርጅታችን የሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍና የግብአት አቅርቦት በጋራ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ያስችላል ብለዋል፡፡
በርክክቡ ወቅት የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲንን ጨምሮ የዘርፉ ተመራማሪዎችና በኢትዮጵያ የቪታ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት