የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ከተለያዩ አጋር አካላት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ2ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የቆዳ ጤና ቀንን በተለያዩ መርሐ ግብሮች አክብሯል። የበዓሉ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ዛሬ ሐምሌ 1 / 2017 ዓ/ም ተካሂዷል::ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ቆዳ ታሪካችንን፣ አካባቢያችንን፣ ጤናችንን ፣ እና የስሜታችንን ሁኔታ የሚያንጸባርቅ የሰውነታችን የመጀመሪያ መከላከያ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ተገቢውን ትኩረት የማያገኝ የሰውነታችን ወሳኝ ክፍል መሆኑን ተናግረዋል። ሁልጊዜ ቆዳችን የሰውነታችን ውጫዊ ክፍል ብቻ ሳይሆን ውስጣችን የሆነውን ሁኔታ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ማስታወስ ይገባል ያሉት ዶ/ር ተክሉ በትምህርትና ፈጠራ በመታገዝ ይህን አስደናቂ አካል የመንከባከብ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። የቆዳ ጤና ቅድሚያ የሚሰጥበት የወደፊት ዘመን እንዲፈጠር የዚህ ዓይነት መድረኮችና የዘመቻ ሥራዎች ወሳኝ ሚና ያላቸው መሆኑን የገለጹት ም/ፕሬዝደንቱ ይህ ሁነት በአርባ ምንጭ እና በአካባቢው እንዲከበር የበኩላቸውን ለተወጡ የኮሌጁና የምርምር ማዕከሉ የሥራ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ በ 2017 የትምህርት ዘመን እንደ ኮሌጅ በሁሉም መስክ ስኬቶች የተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸው በቅርቡ በሁለት ፕሮግራሞች የተገኘውን ሀገር አቀፍ እውቅና ለአብነት ጠቅሰዋል። በኮሌጁ በዚህ ዓመት 50 የምርምር ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ደስታ ከነዚህም መካከል አስሩ የትብብር ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ገልጸዋል:: ትኩርት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል በቆዳ በሚገለጹ የተዘነጉ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ላይ በማተኮር ዘርፈ ብዙ የምርምር እንዲሁም ማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል ያሉት ዳይሬከተሩ ይህን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበርን በዓል ለማስተናገድ መቻላችን ትልቅ ዕድልና ስኬት እንዲሁም በቀጣይ በዘርፉ ሊሰሩ ለሚታሰቡ ትልልቅ ሥራዎች መሠረት የሚጥል መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የቆዳ ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዝደንት ዶ/ር ሺመልስ ንጉሴ በዕለቱ ባስተላለፉት ቁልፍ መልዕክት የቆዳ በሽታዎች ጉዳይ በጤና ሥርዓት ውስጥ ትኩረት የተነፈገው ዘርፍ ሲሆን ለዚህም ትክክለኛ የቆዳ በሽታዎች ጫና የሚታወቅ አለመሆኑን በምሳሌነት አንስተዋል። የቆዳ ጤና ቀንን ማክበር ብቻውን በቂ አለመሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሽመልስ የቆዳ በሽታ ችግሮች በማኅበረሰብ ላይ የሚስከትሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት የምናረግበትና ሰፋፊ የግንዛቤ ሥራዎችን የምንሰራበት ሊሆን እንደሚገባ አውስተዋል፡፡
በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ዳይሬክተር ረ/ፕ አብነት ገ/ሚካኤል በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበር ሲሆን የምርምር ማዕከሉ በዓሉን የማክበር ዕድል ያገኘው በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደረገ ውድድር አሸንፎ መሆኑን ገልጸዋል። በዓሉን ምክንያት በማድረግ በጋሞ ዞን ቆጎታ ወረዳ እና አርባ ምንጭ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሰራታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ በተጨማሪም የቆዳ በሽታ ልየታን ጨምሮ በሁለቱም አካባቢዎች 350 ለሚያህሉ ታማሚዎች ሕክምና መስጠቱን ተናግረዋል።
በምርምር ማዕከሉ ተባባሪ ተመራማሪ የሆኑት ዓለማየሁ በቀለ በቆዳ ላይ በሚገለጹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎችን አስመልከተው ባቀረቡት ገለጻ በዓለማችን ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎች ትኩረት በሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች የሚጠቁ ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት በዚህ ዘርፍ ከለያቸው 22 በሽታዎች መካከል 10 ከመቶው በቆዳ ላይ የሚከስቱ መሆናቸውን ገልጸዋል። እነዚህ በሽታዎች በአብዛኛው የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ የገጠር የኀብረተሰብ ክፍሎችን የሚያጠቁ መሆኑን የጠቀሱት ተመራማሪው ማዕከሉ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን በሽታዎቹን ከመለየት ባሻገር ተጨማሪ የተግባር ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል::
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የቆዳ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር በረከት አድማሱ በዓለማችን ሶስት ሺህ የሚያህሉ የቆዳ ላይ በሽታዎች መኖራቸውን ገለጸው እ.አ.አ 2019፤ 98, 522 ሰዎች በቆዳ በሽታዎች ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል ብለዋል። በሀገራችን የቆዳ ጤና ጉዳይ ትኩረት የተነፈገው መስከ ሲሆን በኢትዮጵያ ያሉ የቆዳ ስፔሻሊስት ሐኪሞች ቁጥር 200 ብቻ መሆኑንና ከነዚህም መካከል 70 ከመቶው በአዲስ አበባ የሚሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል:: ይህም የዘርፉን ችግር የሚያሳይ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር በረከት የቆዳ ላይ በሽታዎች እንደ ሀገር እያስከተሉ ያሉትን የጤና ችግሮችን ከግንዛቤ በመስገባት ዘርፉ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።
በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ በቀረቡ ገለጻዎችን ተከተሎ የተለያዩ ጥያቄዎችን አስተያየቶች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በመርሐ ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ፣ ተመራማሪዎች ፣ ከአርባ ምንጭ ከተማ እና ከጋሞ ዞን አስተዳደር ጤና ጽ/ቤትና መምሪያ የተወጣጡ ባለድረሻ አካላት ተገኝተዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት