የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ከኦክስፎርድ ብሩክስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እንዲሁም በጀርመኑ "ገርዳ ሄንከል ፋውንዴሽን" (Gerda Henkel Foundation) በገኘው የገንዘብ ድጋፍ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል የቤት ግንባታ ፕሮጀክት እያከናወነ ይገኛል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ባለድርሻ አካላት ሐምሌ 2018 . በቦታው ተገኝተው የፕሮጀክቱን አፈጻጸም የገመገሙ ሲሆን፣ በቀጣይ ቀሪ ሥራዎች ላይም የጋራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ይህ በኮንሶ ዞን ካራት ዙሪያ ወረዳ ገላቦ ቀበሌ በአሽኮ ንዑስ መንደር ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው ፕሮጀክት፣ 100 ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ የተጀመረ ነው። የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት / ተክሉ ወጋየሁ የሕግ ትምህርት ቤቱ በማህበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ ትልቅ ሥራ እያከናወነ መሆኑንና ይህ 100 ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት የዚሁ ተግባር ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል። የአካባቢውን ማህበረሰብ መደገፍ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ፕሬዝደንቱ፣ ተቋሙ በዞኑ የሚያከናውናቸው ዘርፈ-ብዙ ተግባራት እንዳሉ አስታውሰዋል። በቀደመው የግንባታ ምዕራፍ ከተሠሩ 33 ቤቶች የተገኘውን መልካም ተሞክሮ በመውሰድና ግንባታውን ይበልጥ በማሻሻል ረገድ ትልቅ ዋጋ መከፈሉን ገልጸው፤ ቀሪ ሥራዎች በተጀመረው ፍጥነት በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ተጠቃሚዎች በአዲሱ ዓመት በአዲስ ተስፋ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ የሥራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ጉድኝትና ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር / ቶሌራ ሴዳ በበኩላቸው፤ በሕግ ትምህርት ቤት በኩል ማህበረሰቡን ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት የማህበረሰብ ጉድኝት ሥራ ዋነኛ አካል መሆኑን ገልጸው፣ ትምህርት ቤቱ ያሳየው የተቀናጀና ብርቱ ጥረት በተቋም ደረጃ ትልቅ ዕውቅና የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል። ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ትልቅ ስኬት መሆኑን የገለጹት / ቶሌራ፣ የተጀመሩ ሥራዎችን በጥራት በማጠናቀቅ ሌሎች ተጨማሪ የድጋፍ ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኮንሶ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራቾ ጎስጌ ነዋሪዎቹ ላለፉት አራትና አምስት ዓመታት በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ በማለፍ ለከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተጋልጠው እንደነበር አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት ግን አብዛኞቹ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለስ መቻላቸውን ጠቁመዋል። ይህ የቤት ግንባታ ፕሮጀክት ትልቅ ተስፋ የሚሰጥና የህሊና ዕርካታን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፣ የዞኑ አስተዳደር ግንባታው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ቃል ገብተዋል።

የሕግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አብረሃም ክንፈ በበኩላቸው፤ ሥራው በርካታ አስቸጋሪ የግዥ ሂደት ተግዳሮቶችን አልፎ አሁን ላይ ለተጠቃሚዎች ተስፋ በሚሰጥ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል። ተፈናቅለው በየጫካውና በየጥሻው ይኖሩ የነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ለመመለስ በከፍተኛ ትጋት እየተሠራ መሆኑንና በቀጣይ ጥቂት ወራት ግንባታውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የጥበብ ምንጭ!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት