የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከIBRO እና DANA ፋውንዴሽኖች ጋር በመተባበር የአንጎል ግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንትን ምክንያት በማድረግ ለኮሌጁ መምህራን፣ ተመራማሪዎችና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች እንዲሁም ለመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከታኅሣሥ 12-16/2013 ዓ.ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
የአዕምሮ ጤና ምንነት፣ የአዕምሮ ጤና እድገት እና የአዕምሮ ጤናን የሚጎዱ ሱሶችና አደንዛዥ ዕጾች የሥልጠናው ይዘቶች ናቸው፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ወይንእሸት ገብረፃዲቅ እንደገለጹት የመሰናዶ ተማሪዎች የነገ ሀገር ተረካቢና ትውልድን የሚተኩ በመሆናቸው ስለአዕምሮ ጤና ምንነትና ዕድገት ለማሳወቅ፣ ሱስ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ከወዲሁ ተረድተው የአዕምሮ ጤናቸውን እንዲጠብቁና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ለማስተማር እንዲሁም በአካባቢያቸው ላሉ ወጣቶች ያገኙትን ትምህርት በማስተላለፍ ትውልድን ከሱስ አደጋ ለመታደግ የተዘጋጀ ሥልጠና ነው፡፡
በኮሌጁ የፋርማኮሎጂ ት/ክፍል መምህር ዶ/ር ሳምሶን ሳህሌ ሥልጠናው በሥነ-አዕምሮ ሳይንስ ዙሪያ የተሠሩ ምርምሮችን በማቅረብ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ፍላጎት ያላቸው ወደ ሙያው እንዲገቡ ለማበረታታትና ሙያውን ለማስረጽ ብሎም የሱስ አስከፊነትን ተረድተው ራሳቸውን እንዲጠብቁና ወደ ሱስ የገቡም ካሉ ለመውጣት የሚያስችላቸውን አቅጣጫ ለማሳየት የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአንጎል ግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚከበር መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሳምሶን ሣምንቱን አስመልክቶ የሚዘጋጁ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በተከታታይነት ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ሌላኛው የት/ክፍሉ መምህር አቶ ብሩክ ሰይፉ በበኩላቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ለመዝናናት፣ ከጭንቀት ለመውጣትና ጊዜን ለማሳለፍ ሲሉ ለጫት፣ ሲጋራ፣ አልኮል፣ ሺሻ፣ ሃሺሽና ለመሳሰሉ ሱሶች እንደሚዳረጉ ተናግረው ይህም ለኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ለተለያዩ የጤና ቀውሶች የሚዳርግ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ወጣቱ ይህን ከወዲሁ ተረድቶ ከሱስ በመራቅ ሕይወቱን በአግባቡ እንዲመራ ለማስቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው መዘጋጀቱን መምህር ብሩክ ገልጸዋል፡፡
ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት በሥልጠናው በመሳተፋቸው መደሰታቸውንና ጠቃሚ መረጃ ማግኘታቸውን ተናግረው ሱስ ለጊዜው አዕምሮን የሚያነቃቃ ቢሆንም አደጋው የከፋ በመሆኑና ማኅበረሰቡ ከሱስ ነጻ ቢሆን የተስተካከለ ዕድሜና ኑሮ ሊኖረው እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት